Nehemiah 6

በቅጥሩ ሥራ ላይ የተነሣ ሌላ ታቃውሞ

1እስከዚያች ጊዜ ድረስ ለበሮቹ መዝጊያ ባልገጥምላቸውም እንኳ፣ ቅጥሩን መሥራቴንና የቀረ ክፍት ቦታ አለመኖሩን ሰንባላጥ፣ ጦብያ፣ ዐረባዊው ጌሳምና የቀሩትም ጠላቶቻችን በሰሙ ጊዜ፣ 2ሰንባላጥና ጌሳም፣ “ናና በኦኖ ሜዳ ከሚገኙት መንደሮች
የዕብራይስጡ ቅጅ፣ ኬፍሪም ይላል።
በአንዲቱ እንገናኝ” ሲሉ ይህችን መልእክት ላኩብኝ። እነርሱ ግን እኔን ለመጕዳት ዐቅደው ነበር።
3እኔም፣ “ታላቅ ሥራ እየሠራሁ ስለሆነ፣ ወዳላችሁበት ስፍራ መውረድ አልችልም፤ ትቼው ወደ እናንተ ወርጄ ሥራው ለምን ይቆማል?” በማለት ይህን መልስ የሚያደርሱ መልእክተኞችን ወደ እነርሱ ላክሁ።

4አራት ጊዜም ይህንኑ ዐይነት መልእክት ላኩብኝ፤ እኔም በእያንዳንዱ ጊዜ ያንኑ መልስ ሰጠሁ።

5ከዚያም ሰንባላጥ ለአምስተኛ ጊዜ ያንኑ መልእክት በረዳቱ ላከብኝ፤ በእጁም ማኅተም የሌለው ያልታሸገ ደብዳቤ ይዞ ነበር፤ 6የተጻፈበትም እንዲህ የሚል ነበር፤

“አንተና አይሁዳውያን ለማመፅ እንደምትዶልቱና ቅጥሩንም እንደምትሠሩ በሕዝቦች መካከል ተወርቷል፤ ጌሳምም እውነት መሆኑን አረጋግጧል፤ ከዚህም በተጨማሪ በተወራው መሠረት አንተ ንጉሣቸው እንደምትሆን፣
7ስለ አንተም ‘በአይሁድ ንጉሥ አለ’ ብለው በኢየሩሳሌም የሚያውጁ ነቢያትን እንኳ ሳይቀር እንደ ሾምህ ተወርቷል፤ ይህም ነገር ለንጉሡ መድረሱ አይቀርም፤ ስለዚህ መጥተህ በአንድነት እንመካከር።”

8እኔም “አንተ የምትለውን የመሰለ ምንም ነገር አልተደረገም፤ ይህ አንተ በአእምሮህ የፈጠርኸው ነው” ብዬ መልስ ላክሁበት።

9ሁሉም፣ “እጃቸው መሥራት እስኪሳነው ድረስ ይዝላል፤ ሥራውም ሳይጠናቀቅ ይቀራል” ብለው በማሰብ ሊያስፈራሩን ሞከሩ። እኔ ግን፣ “አሁንም እጄን አበርታ” ስል ጸለይሁ።

10አንድ ቀን ቤቱ በላዩ ላይ ተዘግቶበት ወደ ነበረው ወደ መሔጣብኤል ልጅ ወደ ድላያ ልጅ ወደ ሸማያ ሄድሁ፤ እርሱም፣ “ሰዎች ሊገድሉህ ይመጣሉ፤ በርግጥም በሌሊት ሊገድሉህ ይመጣሉ፤ በእግዚአብሔር ቤት ባለው በቤተ መቅደሱ ውስጥ እንገናኝ፤ የቤተ መቅደሱንም በሮች እንዝጋቸው” አለኝ።

11እኔ ግን፣ “እንደ እኔ ያለ ሰው ሸሽቶ ይደበቃል? ወይም ደግሞ ሕይወቱን ለማዳን ሲል ወደ ቤተ መቅደስ መግባት ይገባዋልን? አልሄድም!” አልሁ። 12በእኔ ላይ ትንቢት የተናገረው ጦብያና ሰንባላጥ በገንዘብ ስለ ደለሉት እንጂ እግዚአብሔር ወደ እኔ እንዳልላከው ተረዳሁ። 13በገንዘብ የተገዛው እኔን ለማስፈራራት ነው፤ ይኸውም ይህን በመፈጸም ኀጢአት እንድሠራና በዚህም መጥፎ ስም ሰጥተው ተቀባይነት እንዳይኖረኝ ለማድረግ ነው።

14አምላኬ ሆይ፤ ስለ ፈጸሙት ድርጊት ጦብያንና ሰንባላጥን ዐስብ፤ ሊያስፈራሩኝ የሞከሩትን ነቢያቱን ኖዓድያንና ሌሎቹን ነቢያትም ዐስብ።

የቅጥሩ ሥራ መጠናቀቅ

15ቅጥሩም ኤሉል በተባለው ወር ሃያ አምስተኛ ቀን፣ በአምሳ ሁለት ቀን ውስጥ ተጠናቀቀ። 16ጠላቶቻችን ሁሉ ይህን ሲሰሙ፣ በዙሪያችን ያሉ አሕዛብ ሁሉ ፈሩ፤ በራሳቸው መተማመንም አልቻሉም፤ ምክንያቱም ይህ ሥራ የተከናወነው በአምላካችን ርዳታ መሆኑን ተገንዝበዋል።

17በዚያን ጊዜ የይሁዳ መኳንንት ለጦብያ ብዙ ደብዳቤ ይልኩ ነበር፤ ከጦብያም መልስ ይላክላቸው ነበር። 18በይሁዳ የሚኖሩ ሰዎች ምለውለት ነበር፤ ምክንያቱም የኤራ ልጅ የሴኬንያ አማት ከመሆኑም በላይ ልጁ የሆሐናን የሌራክያን ሴት ልጅ አግብቶ ነበር። 19ከዚህም በተጨማሪ ስለ መልካም ሥራው በየጊዜው ይነግሩኝና እኔም ያልሁትን ይነግሩት ነበር፤ ጦብያም እኔን ለማስፈራራት ደብዳቤ ይልክብኝ ነበር።

Copyright information for AmhNASV